የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የሱዳን ባለሃብቶች ፌዴሬሽን ተባብረው ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ሰነዱ የሁለቱ አገራት ባለሃብቶችን በቅንጅት መሰራት የሚያስችላቸው ሲሆን በአገራቱ መካከል ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ያሳድጋል።
ሰነዱ የተፈረመው በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ ማዕከል የኢትዮ ሱዳን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በተካሄደበት ወቅት ነው።
የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የአገር አቀፍ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር እና የሱዳን ባለሃብቶች ፌዴሬሽን ኃላፊ ዋግዲ መረጋጊ ማህጉብ ናቸው።
የግሉ ዘርፍ በአገራቱ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የጎላ ድርሻ እንዲኖረው ከማስቻል ባለፈ ባለሃብቶቹ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት በመለዋወጥ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል የአዲስ አበባ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤቱ ፕሬዝዳንት፡፡
ዋግዲ በበኩላቸው የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ከቀረጥ ነፃ የንግድ ቀጣናንና የሱዳን ወደብን በጋራ በመጠቀም፣
የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በማቅረብና በቱሪዝም ዘረፍ ላይ በጋራ በመስራት ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን የተፈራረሟቸውን
ስምምነቶች መሰረት በማድረግ ባለሃብቶቹ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ
ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብረሃቶም መለሰ በበኩላቸው የተፈረመው የመገባቢያ ሰነድ ወደ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ
የሚገቡትን ሱዳናውያን ባለሃብቶች ስለሚያሳድግ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን
ኢዜአ ዘግቧል።